Friday, December 25, 2015

ኢህኣዴግ በስልጣን እስካለ ድረስ ሙስና ከሃገር ኣይጠፋም።



እንደሚታወቀው በቅርቡ በአገር ውስጥ ገቢና በጉሙሩክ አገልግሎት መስሪያ ቤት የሚሰሩ ጥቂት ባለ ስልጣኖችና ተባባሪ የተባሉ ግለሰብ ነጋዴዎች። በሙስና ተወንጅለው ወህኒ መውረዳቸውን ተከትሎ። ገዢዉ ስርኣት ኢህኣዴግ ፀረ-ሙስና ድርጅት ለመምሰል ጥሩምቧ በመንፋት ይገኛል። አንዳንድ የዋህ ዜጎች ይህን ጥሩምቧ በመስማት ገዢው ስርአት ሙስናን ለማጥፋት ዘመቻ የጀመረ መስሏቸው ተስፋ ሲያደርጉ ይታያሉ። ይህ ደግሞ ስርአቱ ከማን አለብኝነት ተግባሩ የተነሳ እንጂ እውነት የኢህአዴግ መንግስት ሙስናን ተጠይፎ ከአገር ሊያጠፋው የተነሳሽነትና የቆራጥነትን ወኔ ተላብሶ በሙሰኞች ላይ የፖለቲካ ጡንቻ ሊያሳርፍባቸው አስቦ አይደለም፣
በመሰረቱ ሙስና በወያኔ ስርአት ውስጥ የስርአቱ ዋነኛ መቆሚያ ምሰሶ ከሆነ ውሎ አድሯል። በአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት እየተመናመኑ በሄዱበት ፍጥነት ነው ሙስና እየደራ የሄደው። ከላይ እስከታች በተዘረጋው የወያኔ ስርአት ውስጥ ከቁንጮ ባለ ስልጣናት እስከታችኛው አገልጋይ ካድሬዎች ድረስ በሙስና ያልተዘፈቀ የስርአቱ አገልጋይ መፈለግ “ከዝንጀሮ ቆንጆ የመምረጥ” ያህል ከባድ ሆኖ እናገኘዋለን፣
የኢህኣዴግ ትላልቅ ሙሰኞች ለመሸፈን ትንንሽ ሙሰኞችን አልፎ አልፎ በማሰር ፀረ-ሙሰኛ መስለው ሊያሞኙን ቢሞክሩ ዛሬ የመጀመሪያቸው አይደለም። አበው “የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” እንዳሉት። ገዢዉ ብዱን ሳያፍር በድፍረት ሙስና ለማጥፋት ተነሳስቻለሁ በማለት የሙስናን ክስ የሚጠቀምበት። አንድም በውስጡ ካፈነገጡ ሃይሎች ጋር የፖለቲካ ልዩነትን ሲፈጥሩ ሂሳባቸው ለማወራረጃ ወይም ለውጭ ለጋሾች ሙስናን የሚጠላ መስሎ ለመታየት ሲፈልግ ብቻ መሆኑን ከልምድ እና ከተግባሩ ህዝቡ በደምብ ያውቀዋል፣
ያለ ህዝብ ድጋፍ ስልጣን ተቆጣጥሮ የሚገኝ ገዢዉ ስርዓት አገሪቱን ወደ ድህነት ማቅ ቁልቁል እያስገባና አገሪቱ በእዳ እከተተ፣ በአንፃሩ ግን የስርአቱ ቁንጮ ባለ ስልጣናት በሙስና ተዘፍቀው፤ ከየት መጣ የማይባል ሃብት ሰብስበዉ፤ ባለ ፀጋ ሁነዉ ከብረው፤ ራሳቸውን ከሙስና ነፃ ሆኖው ለመታየት ሲያሻቸው ደግሞ ግልገሎቹን በማሰር እና በራሳቸው ሚዲያ አስረሽ ምችው ሲጨፍሩ ውለው ያድራሉ፣
ይሁን እንጂ ስርአቱ የስልጣን ወንበሩን ከተቆናጠጠበት ጊዜ እስከ አሁን ድረስ ከስርኣቱ ጎን ቆሞ የሚሄድ ሙስና ነው። ኢህኣዴግና ሙስናን፤ ሙስናንና ኢህኣዴግ መለያየት አስቸጋሪም ነው። የኢህአዴግ አባልና ደጋፊ ለመሆን የሚሰበሰበው፤ የሚመለመለው በመንግስት ሃብትና ንብረት ሰዎችን በማባበል ፈርተው የሱን ደጋፊ ለመሆን ፍላጎታቸው የሚያሳዩበት ብቸኛ መላ መሆኑን “አለም ያወቀው ፃሃይ የሞቀው” የስርአቱ ዋና መለያ እንደሆነ ይታወቃል፣
ገዢዉ ፓርቲ በየእለቱ የፖለቲካ ድርጅታዊ ስራውና በምርጫ ጊዜ የሚጠቀመው የመንግስት ገንዝብ፤ ተሽከርካሪ፤ ነዳጅ፤ ቢሮ፤ የሚከፈለው የመንግስት ውሎ አበል፤ የሚገለገልበት የህዝብ ቴሌቪዥን፤ ሬዲዮ፤ ጋዜጣ ወዘተ የመሳሰሉት የሙሰኝነት ኣካሄድ መገለጫ ነው። የመንግስት ስራ እድልን ከተማሩ ዜጎች ሳይቀር እየነጠቀ በፓርቲዉ አባልነት መለኪያ ለተመለመሉ አባሎች የሚሰጠው ኣድላዊ ኣሰራር የሙስና ዉጤት መሆኑ አሁን አሁን ህዝቡን እየተረዳዉ መጥተዋል፣
ኤፈርት፤ ጥረትና ድንሾ የመሳሰሉት የኢህአዴግ ኩባንያዎች ከህዝብና ከመንግስት በተዘረፈ ሃብት መመስረታቸው ሳያንሳቸዉ ትናንት ከባንክ ካለተከራካሪ እየተበደረ የሚነግድብን ንግድ። ሲከስር ብድሩና ወለዱን መክፈል ሲያቅተው ኪሳራውን በድሃው ህብረተሰብ ሊነግድ የሚፍጨረጨር ስርአት መሆኑን ምንኛ የሚዘገንን ነው፣
አሁን ደግሞ የ2007 ዓ/ም የክረምትን ወቅት ተከትሎ በሁሉም በአገራችን አካባቢዎች ሰፊ ድርቅ በተከሰተበት ሁኔታ ህዝቡ በርሃብ አለንጋ እየተገረፈና እየተሰደደ ባለበት ጊዜ። እነዚህ የስርአቱ ኣመራሮች ሆኖው። በህዝብ ስም ግን እየነገዱ ያሉት ድርጅቶች ለዚህ የተራበ ህዝብ ጥያቄ የሚመልሱ ሳይሆኑ በተራበው ህዝብ ስም ከለጋሽ ድርጅቶችና አገሮች የተገኘ ያለውን የእርዳታ እህል ከአፉ ለመቀማት የሚያደርጉት ሽርጉድ የስርአቱ ሙሰኛ ባህሪ የሚያጎላ ከመሆኑም ባሻገር። የተራበው ህዝብ ጎሮሮ ዘግቶዉ የሚቀሙ ብቸና ጥላቶች ሁኖው እናገኛቸዋለን፣
ለማጠቃለል። ስርአቱ እንኳንስ ሙስናና ሙሰኞች ሊያጠፋ ይቅርና ኣዳዲስ ወደ ድርጅቱ የሚመለመሉ ኣመራሮች በሙስና የተቃኙ ካልሆኑ በስተቀር ሙስና የሚቃወሙ ከሆኑ ኣመራር ኣድርጎ ለመሾም ህሊናው አይፈቅድለትም። ስለሆነም ኢህኣዴግ በስልጣን እስካኣለ ድረስ ሙስና ከአገር ሊጠፋ ከቶ አይችልም፣